በተከበሩ ዶ/ር ተስፋዬ ቤልጂጌ የተመራ ልኡካን ቡድን የተለያዪ መርሀ ግብሮችን አካሄደ
ዛሬ ማለዳ ድሬዳዋ የገባው ልኡካን ቡድን የተለያዩ መርሀ ግብሮችን ያከናወነ ሲሆን በመጀመሪያም በሀይስኩል ጋራ በመገኘት ከድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሂደዋል። የመርሀግብሩን የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲህያ አደን እንደተናገሩት በአገር አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር መጪውን የብልጽግና ትውልድ ጠንካራ የበጎ ፍቃድ ስራዎችን እያስተማሩ ከመሄድ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። በአስተዳደር ደረጃም 3 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው በመርሀግብሩም ከድሬዳዋ አልፎ ለጎረቤት አገር ጅቡቲም ጭምር የችግኝ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው በልኡካን ቡድኑ ለተደረገው ትብብርና ድጋፍም በድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ ስም ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመቀጠልም ንግግር ያደረጉት የተከበሩ ዶ/ር ተስፋዬ ቤልጂጌ በአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ስለተደረገላቸው ኢትዮጵያዊነትን የሚያሳይ አቀባበል ከፍተኛ ምስጋናቸውን ገልጸው የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ድሬዳዋን የሰላም የፍቅርና የመቻቻል እና የኢትዮጵያ የአንድነት መገለጫ ከተማ በማድረግ ረገድ እየተሰራ ላለው ስራ እና እየተመዘገበ ላለው ውጤት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እውቅና እንደሚሰጠው ገልጸዋል ። በመቀጠልም በአሸዋ የገበያ ማእከል በደረሰው የእሳት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ የ5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በክረምት በጎፍቃድ ለሚሰሩ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አበርክተዋል።
በመጨረሻም ልኡካን ቡድኑ እና የድሬዳዋ ከፍተኛ አመራሮች የችግረኞችን ቤት እድሳት የማስጀመር መርሀ ግብር አካሂደው በድሬዳዋ አስተዳደር በመሠራት ላይ ያሉ የልማት ስራዎችን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።
30/12/2016 ዓ.ም
ይህን ዜና አጋራ