የአስተዳደሩን አስፈፃሚ እና ህግ ተርጓሚ አካላትን ማቋቋም፣ የተለያዩ ህጎችን ማውጣት፤ የአስተዳደሩን በጀት በመመርመር ማፅደቅ፤ የህብረተሰቡ ችግሮች፣ ጥቆማዎች አቤቱታዎች የሚፈቱበትን ስርዓት መዘርጋት፤ የአስተዳደሩን አካላት በመከታተል፣ በመቆጣጠር አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ በአስተዳደሩ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን እና ልማት እንዲፋጠን ማድረግ ነው፡፡
በ2022 የህግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ ዲሞክራሲ የዳበረባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት እና ለህዝቦቹ ምቹ የሆነች ድሬዳዋን ማየት ነው፡፡
በማንኛውም ሉዓላዊ አገር ውስጥ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ የዲሞክራሲ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ ዕኩልነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጡ ከሚያደርጉና የላቀ ሚና ከሚጫወቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ተቋማት መካከል በግንባር ቀደም የሚጠቀሰው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ታሪክ ከአስር ምዕተ ዓመት የዘለለ ወይም እ.ኤ.አ ከ930 የጀመረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜም አስፈላጊነቱ እየታወቀና እየዘመነ በዘመናችን ላይ ደርሷል፡፡ታሪኩና ትግበራው የጀመረው ከአውሮፓይቱ አገር ስፔን ቢሆንም ዘመናዊነትን በተላበሰ መልኩ መተግበር የጀመረው ግን እ.ኤ.አ በ1295 ወይም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ ውስጥ መሆኑን የሚያስረዱ ሰነዶች ብዙ ናቸው፡፡
የምክር ቤት የአሰራር ሥርዓት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ሰብዓዊ መብት መከበር ያለው አስፈላጊነትና አገራዊ ፋይዳ በምንም የሚተካ አይደለም፡፡ በዚህም ጠቀሜታው በዘመናችን ምክር ቤት የሌላቸው የዓለም አገሮች አሉ ለማለት ያዳግታል፡፡ በአገራችን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታሪክና የአሰራር ሥርዓት ከዘጠና ዓመት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ታሪክ የጀመረውም በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በ1923 ዓ.ም ሲሆን በደርግ ዘመነ መንግስትም ሲተገበር እንደነበረ የሚያስረዱ ሰነዶች አሉ፡፡ በተጠቀሱት ሁለት የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት የተቋቋመውና ሲተገበር የነበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር ሥርዓት ግን ከወቅቱ የፖለቲካና የመንግስት ሥርዓት የመነጨ ስለነበረ ህዝቡ ከተቋሙ የሚጠብቀውን አገልግሎት ለማግኘት ያስቻለ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ይህም የሆነው የም/ቤትን ትክክለኛ አላማ ለማሳካት የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ የሆነ የእንደራሴዎች የምርጫ ሂደትንና የአሰራር ሥርዓት የተከተለ ባለመሆኑ ነበር፡፡ እንዲህ ማለት ግን በቀደሙት ዘመናት የተተገበሩ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአሰራር ሥርዓቶች ለዛሬው ዘመን መነሻ የሆኑ መሰረቶችን አልጣሉም ማለት አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የይዘት፣ የቅርጽ፣ የአላማና የተልዕኮ ለውጥ የታየው በ1987 ዓ/ም የፀደቀውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ከህገ መንግስት መጽደቅ ተከትሎ የተቋቋመውና ለ30 ዓመታት ያህል የተተገበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ከዚህ ም/ቤት መቋቃምና ወደ ሥራ መግባት ጋር ተያይዞ በክልሎች፣ በዞኖች፣ በከተሞችና በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የተቋቋሙ ምክር ቤቶችም ካለፉት ዘመናት በተሻለ ደረጃ ተቋቁመው የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ በማንኛውምና በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ምክር ቤቶች ሥልጣንና ሃላፊነት ተመሳሳይ በመሆኑም ዜጎችን የሚያረኩ ባይሆኑም የህግ የበላይነት የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማፋጠን፤የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማረጋገጥ ፣ወዘተ የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደርም ሆነ በየደረጃው የተቋቋሙ ም/ቤቶችም ለአገራችን የዲሞክራሲ ግንባታ፣ ለዜጎች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ለአገራችን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትም በዜጎች የጎላና የተጠናከረ ተሳትፎ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም የዜጎች ተጠቃሚነት የሚረጋገጠውም ሆነ የህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር የሚሰፍነው በም/ቤታችን ወይም የም/ቤታችን ቋሚ ኮሚቴዎች በሚያደርጉት ጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ይህም ዕውነታ የሚያረጋግጠው የም/ቤቶች ስኬት በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም መልካምና መጥፎ ተግባር የሚፈፀመው ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ነው፡፡ ህብረተሰቡም የተመለከተውን ህገ ወጥ አሰራር ካላጋለጠና መረጃ ካልሰጠ ምክር ቤቱ ሁኔታውን በመገንዘብ ችግሩን የሚቀርፍና የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ህግ ማውጣት አይችልም፡፡
በመሆኑም የምክር ቤታችን አላማና የአገራችን የብልጽግና ጉዞ የሚሳካውም ሆነ የአስተዳደራችን ነዋረዎችም የልማት ዕድሎች ተጠቃሚ የሚሆኑት ምክር ቤታችን በሚያፀድቃቸው የህግ ማዕቀፎች፣ በቋሚ ኮሚቴዎች የክትትልና ቁጥጥር ተግባራት ብቻ አለመሆኑን በመረዳት መላው ህብረተሰብ የነቃ ተሳትፎ ማድርግ ይጠበቅበታል፡፡ አስፈፃሚ አካላትም በአገር አቀፍና በአስተዳደራችን የፀደቁ የህግ ማዕቀፎችንና የም/ቤታችን ቋሚ ኮሚቴዎች የሚሰጧቸውን ግብረ መልሶች አግባቡ በመተግበርና ፈጣን ምላሽ በመስጠት የመራጩን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነትና የአኗኗር ዘይቤ የሚያሻሽሉ አገልግሎቶችን መስጠት ይጠበቅባቸዋል በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
አመሰግናለሁ !