የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት የሆኑት የድሬዳዋ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፣ የድሬዳዋ ብዙሀን መገናኛ ድርጅት እና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች አመራሮችና ሰራተኞች በአለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በጋራ እንታገል በሚል መሪ ቃል በመከበር ላይ ያለውን አለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን አስመልክቶ የፓናል ውይይት በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂደዋል፡፡
የፓናል ውይይቱን በመክፈቻ ንግግር ያስጀምሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጸሀፊ የተከበሩ አቶ ማሪቆስ ባዩህ ሲሆኑ በንግግራቸውም የጸረ ሙስና ቀን ሲከበር በተለያዩ መድረኮች ከብልሹ አሰራርና ከሙስና ጋር ተያይዞ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት በአሰራር እና በሪፎርም በሁሉም ተቋማት የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው ኮሚሽኑ ባዘጋጀው ንቅናቄ መሰረት የተገለጹ ችግሮችና መፍትሄዎች እና ከመንግስት ሰራተኛው የሚጠበቀው ሚና ምንድነው የሚለው ጉዳይ ላይ በተለይም የዲሞክራሲ ተቋማት ሙስናን ከመከላከል አንጻር የጎላ ሚና ስላላቸው ሁሉም አመራርና ሰራተኛ ሚናውን በመለየትና ተነሳሽነትን በመውሰድ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ እንዲሁም ሙስናን ከመታገል አንጻር ህብረተሰቡን የማንቃት ሃላፊነት የአንድ አካል ድርሻ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ አካል እና አጋር አካላት በህብረት ሊሰሩት የሚገባ የጋራ ሃላፊነት ነው ብለዋል፡፡
በመቀጠልም በድሬዳዋ አስተዳር ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አንድነት ሀይሉ የውይይት ሰነድ ቀርቦ በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ጸሀፊ የተከበሩ አቶ ማሪቆስ ባዩህ አወያይነት ውይይት ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል ፡፡
ይህን ዜና አጋራ