• info@ddacouncil.gov.et
  • 025-11-30654
News Photo

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአልን በተለያዩ ፕሮግራሞች ተከበረ

በድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስተባባሪነት "ብዝሐነትና እኩልነት ለሐገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በድሬደዋ አስተዳደር ሲከበር የነበረው 18ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል በዛሬው እለት  በለገሐር አደባባይ በቢል ቦርድ ምርቃት የተጀመረው የማጠቃለያ ፕሮግራም ሲምፖዚየም በተለያዩ ሁነቶች ተካሄዷል።

በሲምፖዚየሙም የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር ፤ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ም/አፈ ጉባኤ፤የአስተዳደሩ ም/ከንቲባ ክቡር አቶ ሀሪቢ ቡህ፤የሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም፤የሀረሪ  ሊግ ም/ሀላፊ  የተከበሩ ወ/ሮ ዚነት ዩሱፍ፤የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት ተወካይ የተከበሩ ወ/ሮ አልፍያ፤የሀይማኖት አባቶች ፤ አባ ገዳዎች፤ኡጋዞች፤የሀገር ሽማግሌዎች፤የካቢኔ አባላት፤ ከፍተኛ የድርጅት አመራሮች እንዲሁም የሴክተር መስሪያ ቤት ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።

የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ም/አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ከሪማ አሊ 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል በድሬደዋ አስተዳደር  "ብዝሐነትና እኩልነት ለሐገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሁነቶች በማክበርና በመንግስት ተቋማቶች ፤ በወጣቶችና ሴቶች መድረክ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ   መድረኮች  በፌዴራሊዝም ስርአት ላይ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር  የመመያያ ሰነድ ቀርቦ  ውይይት ሲካሄድ  መቆየቱን ጠቅሰው ይህ በአል አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በአሉን ከማክበር ባሻገር በምናደርገው የብልፅግና ጉዞ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ለጋራ እድገትና ስኬት እንዲሁም ለሀገረ መንግስት ግንባታችን ወሳኝ ሚና ስላለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዚህ ረገድ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል በማለት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ አቶ ከድር ጁሀር የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፀደቀበት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል ተብሎ በሚያዚያ 21/1998 ዓ.ም መወሰኑ በአሉ በሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲዳብርና በጋራ የመበልፀግ ህልማችንን እውን ለማድረግ ትልቅ ሚና ስላለው 18ኛውን  የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል ስናከብር  ህብረብሄራዊ አንድነታችን በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆም በምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን ሀገርን አንድ አድርጎ፤ሰላሟንና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ የማስቀጠል ህልውና የህልውና ጉዳይ መሆኑን አውቀን ሁላችንም የሚጠበቅብንን የዜግነት ሀላፊነት ለመወጣት ከመቼውም 
ጊዜ በላይ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢኮኖሚ ልማትና ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኃ/ማርያም ዳዲ የሲምፖዚየሙን የመወያያ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት ም/አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ከሪማ አሊና የሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም የውይይት መድረኩን መርተዋል።

በዚህም በድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አስተባባሪነት ሲከበር የነበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአል የተጠናቀቀ ሲሆን እንደሀገር አቀፍ ከህዳር 25 እስከ 29 በጅግጅጋ ከተማ እንደሚከበር ተገልጿል።

 

ይህን ዜና አጋራ

አስተያየት ይስጡ

ለህዝብ እና ለመንግስት ጥቅሞች ቅድሚያ የምንሰጥ ነን!